የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የፌዴራል ገንዘብ ሚኒስቴርን ደብዳቤና ቁጥር ጠቅሶ ለመምሪያዎች ባስተላለፈው መልዕክት የሚኒስቴሩ ደብዳቤ ከወጣበት መጋቢት 06 ቀን 2015 ዓ.ም በፊት የተገባን የአቅርቦት ውል ሳይጨምር የብረታ ብረት፣ የአውቶሞቲቭ እና ኢንደስትሪያል ዘይቶችና ቅባቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡም ሆነ ምርቶች በአገር ውስጥ ሲሸጡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሊሰበሰብ የሚገባ መሆኑን እና ከተጠቀሰው ቀን በፊት የተጻፉ ማስፈፀምያ ደብዳቤዎች እና እነሱን መሠረት ያደረጉ ደብዳቤዎች በአዲስ የተተኩ መሆኑን አሳውቋል።
በመሆኑም የፌዴራል ገንዝብ ሚኒስቴር ባስተላለፈው ሠርኩላር መሠረት የብረታ ብረት፣ የአውቶሞቲቭ እና ኢንደስትሪያል ዘይቶች እና ቅባቶች ወደ አገር ሲገቡም ሆነ በአገር ውስጥ ሲሸጡ ታክስ የሚሰበሰብባቸው መሆኑ ተውቆ የግብይት እንቅስቃሴያቸው ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ያለባቸውን ግብር ከፋዮች እንዲመዘገቡ በማድረግ ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ግብይታቸው ለተጨማሪ እሴት ታክስ ብቁ ያልሆኑትን ተርን ኦቨር ታክስ እንዲሰበስቡ መደረግ እንዳለበት እና መምሪያዎች ማስፈፀምና መፈፀም እንዳለባቸው ታህሳስ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በቢሮው የወጣ ደብዳቤ ያመላክታል።
ስለሆነም እርስዎ የነዚህ ምርቶች አቅራቢ ከሆኑ ደረሰኝ መስጠትዎትን ተጠቃሚም ከሆኑ ደረሰኝ መጠየቅዎን እንዳይዘነጉ እናሳስባለን።